መሬት፣ መሬት፣ ሁለት
Submitted by Admin on Sat, 01/14/2012 - 23:23ፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማርያም
መሬት ማለት ብዙ ነገር ነው፤ ገበሬው መሬት ሲል ለም አፈር ነው፤ ለከብት አርቢው የግጦሽ መሬት ነው፤ መሀንዲሱ መሬት ሲል ደልዳላ ሜዳ፣ ድንጋይና አሸዋ ነው፤ ስለመሬት ስናስብ በግድ ስለዓየር ጠባዩና ስለውሃም እናስባለን፤ ለደላላውና ለኪራይ ሰብሳቢው መሬት ሸቀጥ ነው፤ የመሬቱ መሸጥ የሚጎዳው በኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖሩ ተከታታይ ትውልዶችን ነው፤ ገንዘባቸውን ይዘው ወደሌላ አገር የሚንሸራተቱትን አይደለም፡፡
ኢትዮጵያ ነዳጅ ዘይት ወይም ሌላ ማዕድን ስለሌላት ከቡናና ከቆዳ የበለጠ ገቢ ያስገኛል ተብሎ የተገመተው መሬት ነው፣ መሬትን በመሸጥ ወይም እያከራዩ ኪራይ በመሰብሰብ በመበልጸግ ይቻላል ተብሎ ታስቦአል፤ ለውጭ አገር ሰዎች በማናቸውም መንገድ የመሬት መብትን ማስተላለፍ ውሎ አድሮ አብዛኛውን የኢትዮጵያ ህዝብ የሚያደኸይ እንደሚሆን አያጠራጥርም፤ ጥቂት ሰዎች በጣም እንደሚከብሩም አይጠረጠርም፡፡
