Add new comment

ደቡብ ሱዳን ቀጣይቱ የኢትዮጵያ ፈተና

ደቡብ ሱዳን ከሰሜኑ ጋር እዚህ አዲስ አበባ ላይ ያደረጋቸው የሰላም ስምምነት ለኢትዮጵያ ከሚያስገኘው ጥቅምና ጉዳት አንፃር ምን አንድምታ አለው? የሚለው ለጊዜው በመወያያ አጀንዳነት ገና ወደ አደባባይ አልመጣም፡፡ ኢትዮጵያ ለረጅም አመታት ሁለቱ አገራት በክብ ጠረጴዛ ዙሪያ ተገናኝተው እርቅ ያወርዱ ዘንድ ያደረገችው አስተዋፅኦ ቀላል የሚባል አይደለም፡፡ መቼም የኢትዮጵያ መንግስት ይህንን ሁሉ ዋጋ የከፈለው ለፅድቅ ነው ብለን የምንመፃደቅ አይመስለኝም፡፡ የየትኛውም አገር የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ የመጨረሻ ግቡ የራስን አገር ጥቅም ማስጠበቅ ነው፡፡ የሱዳንና የደቡብ ሱዳን ወደ እርቅ መምጣት አገራችን ያሰላችው ፖለቲካዊም ይሁን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ይኖራል የሚል እምነት አለኝ፡፡ እነዚህ ስሌቶች አንዳንዴ መልካም ጐናቸው ሲያመዝን፤ በተቃራኒው ደግሞ ከተጠበቀው ይበልጥ የከፋ ቀውስ ይዘው የሚመጡባቸው አጋጣሚዎች ይኖራሉ፡፡ ደቡብ ሱዳን አሁን ላይ ሆነን ይሄንን በረከት ይዛ መጥታለች፤ አልያም ይህንን አይነት መርገምት አድርሳለች የምንልበት ወቅት ላይ ባንሆንም፤ ለወደፊቱ አገራችን እነዚህን ሁነቶች አስልታ የምትዘጋጅባቸውን አንዳንድ ነጥቦችን ማየት ተገቢ ነው፡፡
ሙላት ውብነህ እና ዮሐንስ አባተ በጋራ ባሳተሙት ‹‹Ethiopia transition and development in the horn of Africa›› በሚለው መጽሐፋቸው ከአጠቃላዩ የኢትዮጵያን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ መካከል የአንበሳውን ድርሻ የሚወስደውና በዋቢነት ትኩረት የሚያደርገው አፍሪካን በሚመለከት የሰፈረው ሃሳብ ነው፡፡ በተደጋጋሚ እንደተገለጸው በአህጉሪቱ ዘርፈ ብዙ ጉዳዮች ዙሪያ የአገራችንን ንቁ ተሳትፎ ማድረግን ቀዳሚ ግቧ አድርጎ ማስቀመጡ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡
1960 በፊትደከ1960ዎቹ በፊት ኢትዮጵያ አብዛኛውን የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ከምስራቅ አፍሪካ ሀገራት መካከል ከጅቡቲ መንግስት ጋር የነበራት ግንኙነት ተጠቃሽ ነው፡፡ ለዚህም ዋነኛው የግንኙነቱ ምክንያት ሁለቱን ሀገሮች በኢኮኖሚ አስተሳስሮ የያዘው የጅቡቲ አዲስ አበባ የባቡር ሀዲድ መስመር ነው፡፡ ከዚህ ውጭ በጊዜው በቅኝ ግዛት ስር ከነበሩት የጐረቤት ሀገራት ጋር ይህ ነው ሊባል የሚችል አይነት ጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት አልነበራትም፡፡
ከ1960ዎቹ በኋላ ግን አገራችን ከነዚህ አገራት ጋር ከጉርብትና ባለፈ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ቀርፃ ከቀሩት የቀጠናው ሀገራት ጋር ጥብቅ ግንኙነት ልትመሰርት ችላለች፡፡ በጊዜው አገራችን ካከናወነቻቸው ተግባራት መካከል በእንግሊዝና ፈረንሳይ ቅኝ ግዛቶች ፣ በሰሜኑ አረብ አገራትና በተቀረው ጥቁር የአፍሪካ አገራት፣ እንዲሁም በካዛብላንካና በሞኖሮቪያ ቡድኖች መካከል የተነሱትን አምባጓሮዎች ለመፍታት የተጫወተችው ሚና ከፍተኛ ነበር፡፡ ኢትዮጵያ ለየትኛውም ቡድን ወገንተኛ አለመሆኗ የሁሉም አጋር እንድትሆን ከማስቻሉም በላይ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት እ.ኤ.አ. በ1963 ዓ.ም. ሲመሰረት ለመቀመጫነት ተመርጣ ሰፊ የሆነ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጥቅሞችን ለማግኘት ችላለች፡፡ ለዚህም እንደማሳያነት የሚጠቀሰው አፄ ኃ/ስላሴ በ1962 (እ.ኤ.አ) ዓ.ም. በሌጐስ ስብሰባ ላይ‹‹ኢትዮጵያ እራሷን እንደ አንድ ቡድን ብቻ ታያለች ይህም የአፍሪካ ቡድን ብቻ ነው›› ማለታቸው የሁሉም አይን ሀገሪቷ ላይ እንዲያርፍ አስችሏል፡፡
የኢትዮ-ሱዳን ግንኙነት
የረጅሙ የኢትዮ-ሱዳን ታሪካዊ ግንኙነት አንዴ በጥላቻ ሌላ ጊዜ በወዳጅነት ረጅም አመታትን አሳልፏል፡፡ የአፄ ኃ/ስላሴ መንግስት መውደቅ፤ በተለይም በ1956 ዓ.ም. (እ.ኤ.አ) የሱዳን መንግስት ነፃ መውጣትን ተከትሎ በሁለቱ አገራት ውስጥ የተገንጣይ ቡድኖች መስፋፋት፤ የድንበር ማካለልና የስደተኞች ጉዳይ ለግንኙነቱ እንደ ዋነኛ ችግር ፈጣሪ ተደርገው የሚቆጠሩ ነበሩ፡፡
በኢትዮጵያ የሰሜኑ የኤርትራ ክፍል የፌዴራል ስርዓቱ መጣስና የኃ/ስላሴን የውህደት ፖሊሲ በመቃወም የተነሳው የተገንጣይ ቡድን አንዱ ሲሆን፤ በሱዳን ደግሞ የደቡብ ክፍል ከሰሜኑ አረብ አስተዳደር ጋር ባለመስማማት ነፍጥ ማንሳቱ በሁለቱ አገራት ፖለቲካዊ ግንኙነት ላይ የራሱን አሻራ ሊያስቀምጥ ችሏል፡፡ የኤርትራ ገንጣይ ቡድን የነበረው የጀብሐ አመራር ክፍል በአብዛኛው ከእስልምና ሃይማኖት ጋር የተያያዘ በመሆኑ የአረብ አገራትን ቀልብ ለመግዛት አስችሎት ነበር፡፡ ለዚህም የ‹‹እስልምና ወንድማማችነት›› በሚለው የአጋርነት ፖሊሲ ምክንያት የሰሜኑ የሱዳን ክፍል የኤርትራ ተገንጣይ ቡድኖችን በከፍተኛ ሁኔታ መርዳት ጀመረ፡፡ ይህን አስመልክቶ አቢር ሞርደካይ “The continuous horn of Africa conflict” በሚለው መጽሐፋቸው ኢትዮጵያ ከአረቡ አገራት ጋር በመቆራረጥ በአዲስ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ አቅጣጫ ፊቷን ወደ እስራኤል ማቅናቷን ያብራራሉ፡፡ ‹‹ከዚህ በኋላ ነበር የአረቡ ሀገራት አጋርነት ከሃይማኖት በተጨማሪም የፖለቲካዊ ግንኙነት መልክ እየያዘ የመጣው›› ሲሉ አክለው ያብራራሉ፡፡
ይህን ተከትሎ ነበር የኢትዮጵያ መንግስት የሰሜኑን አረብ አገዛዝ ለማዳከም የደቡብ ሱዳን ግዛት (በአብዛኛው ክርስቲያን እንደሆነ የሚታመነው) ያነሳውን የአኒያ-ኒያ (Anya-Nya) እንቅስቃሴ መደገፍ የጀመረው፡፡ ሁለቱም ሀገሮች የውክልና ጦርነት (Proxy war) በማድረግና ተቃራኒ ቡድኖችን በመደገፍ እልህ ውስጥ የገቡት እንዲህ ብለው ነው፡፡
ይህንንና የመሳሰሉትን ሸካራ ግንኙነቶች አልፈው አሁን ኢትዮጵያ ሱዳን ድረስ ዘልቃ የሀገሪቱን ሰላምና ፀጥታ ለማረጋጋት የምታስፈልግበት ጊዜ ደረሰ፡፡ ደቡብ ሱዳንም ከሽምቅ ውጊያ ተላቃ ወደ አገር አደገች፡፡
ጋምቤላ-ደቡብ ሱዳን
በኢትዮጵያ እና በደቡብ ሱዳን ህዝቦች መካከል ወደፊት ሊፈጠር ስለሚችለው የሁለትዮሽ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ትስስር ለመረዳት ሁለት መንገዶች አሉ፡፡ ቀዳሚው ሁለቱ አገራት ከዚህ ቀደም የነበራቸውን የፖለቲካ-ታሪክ (Political History) በሚመለከት አጭር ዳሰሳ ማድረግ ሲሆን፤ በሁለቱ አገራት ድንበር አካባቢ ያሉትን ህዝቦች ነባር ግንኙነት መስመር ማጥናት ሌላኛው አማራጭ ነው፡፡
በማንኞቹም አገራት የሚኖሩ ድንበር ተጋሪ ህዝቦች የሚያመሳስላቸው አንድ እውነት አለ፡፡ ይህም የጋራ ቋንቋ፣ ባህል፣ የአየር ንብረት፣ የኢኮኖሚ ምንጭና ተመጋጋቢ የህዝብ ለህዝብ ትስስሮሽ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ በዙሪያዋ ከበዋት ካሉ የቀንዱ አባል አገራት ጋር ተመሳሳይ የሆነ ተሞክሮ አላት፡፡ ለምሳሌ በትግራይና ኤርትራ፣ በአፋርና ጅቡቲ፣ በኢትዮጵያ ሶማሌና በሱማሊያ፣ በኢትዮጵያ ሞያሌ እና ኬንያ ሞያሌ እያልን መዘርዘር እንችላለን፡፡
የደቡብ ሱዳንና የጋምቤላ ተሞክሮም ተመሳሳይ ነው፡፡ ስለአገራቱ ህዝቦች ቀጣይ እጣ ፋንታ ለመናገር አስቀድሞ በሁለቱ አገራት ህዝቦች መካከል ያለውን አንድነት እና ልዩነት በሚገባ መመርመር ተገቢ ነው፡፡ አሌክሳንደር ሜኬልበርግ “Changing Ethnic relations, a preliminary investigation of Gambella, south west Ethiopia” በሚለው ጥናታዊ ፅሁፋቸው የጋምቤላን ህዝቦች አሰፋፈር ከደቡብ ሱዳን አንፃር አስተያይተው ያቀርባሉ፡፡ በጥቅሉ በጋምቤላ ውስጥ ወደ አምስት የሚጠጉ ብሔሮች ይገኛሉ (አኙዋክ፣ ኑዌር፣ መጀንገር፣ ኦፓ እና ኮሞ)፡፡ ከነዚህ አምስቱ ብሔሮች መካከል ኑዌር 40% የሚሆነውን አብዛኛውን ድርሻ ሲወስድ አኙዋክ 25%፣ መጀንገር 10% የሚሆነውን ይዘው በተከታይነት ተቀምጠዋል፡፡
በደቡብ ሱዳን ውስጥ ከሚገኙ ህዝቦች መካከል ኑዌር እና አኙዋክ ትልቁን ድርሻ ይወስዳሉ፡፡ የእነዚህ ህዝቦች በሁለቱ አገራት ውስጥ ያላቸው ተዋፅኦ በተናጠል ማየት እንችላለን፡፡ አብዛኛው የኑዌር ተወላጆች ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ቁጥራቸው የበዛ ሲሆን የቀረው ደግሞ በደቡብ ሱዳን ውስጥ የሚገኘው ነው፡፡ በተቃራኒው አብዛኛው የአኙዋክ ቤተሰቦች በደቡብ ሱዳን ሲገኝ የተቀረው የብሔሩ አባላት በጋምቤላ ውስጥ የሚኖሩትን ይጠቀልላል፡፡ ይህ ማለት በሁለቱ አገራት መካከል ተመሳሳይ የሆኑ ህዝቦች በተለያየ መጠን፣ በተለያየ አስተዳደር ስር ይኖራሉ ማለት ነው፡፡
ሰማያዊ ወርቅን በጥቁር ወርቅ
እንደ ተቀሩት የቀንዱ አገራት ሁሉ ደቡብ ሱዳንና ኢትዮጵያን የሚያመሳስላቸው ብዙ መለኪያዎችንም ማስቀመጥ ይቻላል፡፡ ሁለቱም ለህዝባቸው ሊያሟሉ የሚገባቸው ነገር ግን ያልቻሏቸው በርካታ ጐደሎ ነገር አላቸው፡፡ ሁለቱም በመካከለኛው የአገራቸው ክፍልና በድንበር አካባቢ ያሉ ህዝቦቻቸው እጅግ የተራራቁ ከመሆናቸው በተጨማሪ ለተቀረው የአገሬው ነዋሪ የምግብና የኃይል አቅርቦትን በበቂ ሁናቴ ለማዳረስ የተሳናቸው ናቸው፡፡ ስለዚህ እነዚህን ችግሮቻቸውን ለማስታረቅ ሁለቱም የግድ ተቀራርበው ሊሰሩባቸው የሚገቡ መደላደሎች መኖራቸው እሙን ነው፡፡
ኢትዮጵያ ከደቡብ ሱዳን ጋር ወደፊት ለሚኖራት የጠበቀ ትስስር ስትል የሰሜኑን ወዳጅነት ማበላሸት እንደሌለባት ይታመናል፡፡ ለዚህም አንዱ ምክንያት ከሰሜኑ የምናገኘው የወደብ አገልግሎትና እስከዛሬም ድረስ ጥገኛ የሆንበት የነዳጅ አቅርቦት ከዋነኞቹ መካከል ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ሃርይ ቬርሆቨን “The case of regional energy integration: blue gold for black gold” በሚለው ፅሁፋቸው ኢትዮጵያ በተለይ ከሱዳን ጋር ያላትን አዎንታዊ ቁርኝት በሰፊው አብራርተዋል፡፡ እንደ እርሳቸው አገላለፅ ከሆነ በኢትዮጵያና ኤርትራ መንግስት መካከል የተፈጠረውን ግጭት ተከትሎ ኢትዮጵያ በኤርትራ ትገለገልበት የነበረው የወደብ አገልግሎት በመቋረጡ ምክንያት ፊቷን ወደ ጅቡቲና ሱዳን እንድታዞር ተገዳለች፡፡ ስለዚህ ፖርት ሱዳን ከጅቡቲ ቀጥሎ ሌላኛው የወጪና ገቢ ንግድ ማስተንፈሻ በመሆን እያገለገለ ይገኛል፡፡ ለዚህም ነው ደቡብ ሱዳንን ለማትረፍ በሚል የምንመርጠው አካሄድ ከሰሜን ሱዳን የምናገኘውን የወደብ አገልግሎት እንዳያስተጓጐል መጠንቀቅ ይገባል የምለው፡፡
ሁለተኛው የኢትዮጵያና ሱዳን ጥብቅ ቁርኝት የሚስተዋለው ጥቁሩን ወርቅ (ነዳጅ) በሚመለከት ሁለቱ አገራት የተጓዙበትን መንገድ በማየት ነው፡፡ ምንአልባት መረጃዎቹ ተተንትነው የቀረቡበት መንገድ ይለያይ ይሆናል ሰእንጂ በመግባቢያ ደረጃ ኢትዮጵያ ከ85-90% የሚሆነውን የነዳጅ ፍላጐት የምታሟላው በቀጥታ ከጐረቤት አገር ሱዳን ነው፡፡ ሁለቱ አገራት በደረሱበት ስምምነት መሰረት ሱዳን ለኢትዮጵያ የምታቀርበው ነዳጅ በዋጋ ደረጃ ከአለም መገበያያ አንፃር ሲታይ ዝቅተኛ የሚባል ነው፡፡ ይህ ግብይት በዓመት ከ1.2 እስከ 2 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ሲሆን፤አገራችን በጠቅላላው ከውጭ ንግድ ከምታገኘው ገቢ ሃምሳ በመቶ (50%) የሚሆነውን ነዳጅ ለመግዛት ታውለዋለች፡፡
በቀጣይ የአገራችን ነዳጅ የማግኛ እጣ ፈንታ ወደ ደቡብ ሱዳን የሚያጋድል ይመስላል፡፡ ኢትዮጵያ ለደቡብ ሱዳን መመስረት ቀጥተኛ ተሳትፎ አድርጋለች፡፡ ደቡብ ሱዳን በበኩሏ ኢትዮጵያ አባይን በተመለከተ በምትወስደው ማናቸውም እንቅስቃሴዎች ቅር እንደማትሰኝ መሪዎቿ በተደጋጋሚ ገልፀዋል፡፡ ኢትዮጵያ በአባይ ዙሪያ የምታመነጨው የኤሌክትሪክ ኃይል (ተንታኞቹ ሰማያዊው ወርቅ የሚሉት) ተከትሎ ደቡብ ሱዳን ለህዝቦቿ ከአጭር ርቀት ገዝታ ለመጠቀም ካላት ፍላጐት አንፃር ሁለቱ አገራት በኃይል አቅርቦት ዙሪያ ተመጋጋቢ ግንኙነት ሊፈጥሩ የሚችሉባቸው አማራጮች እየታዩ ይገኛሉ፡፡
አዲሱ ውል
ከደቡብ ሱዳን ግዛቶች መካከል ዩኒቲ፣ የላይኛው አባይ (በደቡብ ሱዳን ድንበር ውስጥ የታጠሩ)፣ እና የአቢዬ ግዛት (የማን እንደሚሆን ገና ውሉ ያለየለት) በነዳጅ ሀብታቸው የሚታወቁ ናቸው፡፡ ይሁንና ደቡብ ሱዳን የምታመርተውን ነዳጅ ለአለም አቀፍ ገበያ ለማቅረብ ይቻላት ዘንድ የምትጠቀመው ብቸኛው የነዳጅ ማስተላለፊያ ቱቦ በሰሜን ሱዳን የሚገኘው ነው፡፡ በቅርቡ ደቡብ ሱዳን ከኢትዮጵያ እና ከጅቡቲ መንግስታት ጋር አዲስ የነዳጅ ማስተላለፊያ ቱቦ ለመዘርጋት በእቅድ ላይ መሆኗን ይፋ አድርጋለች፡፡ የደቡብ ሱዳን ማዕድን ሚኒስትር የሆኑት ስቴፈን ዳዩ ዳኡ አዲሱን ፕሮጀክትና ፋይዳ አስመልክቶ በቀረበላቸው ጥያቄ ስለጠቀሜታው የሰጡት መልስ ሲጠቃለል ሁለት እንዳምታዎች አሉት፡፡
የመጀመሪያው፤ የቀድሞ ነዳጅ ማስተላለፊያ ለመተው (ምንም እንኳን የሶስት አመት ቀሪ ኮንትራት ከሱዳን ጋር ያላቸው ቢሆንም) አዲሱ ፕሮጀክት ተግባራዊ ሲሆን ለደቡብ ሱዳን ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው በመታመኑ የሚነሳ ነው፡፡ አንድም ታሪካዊ ጠላት ከሆነችው ሱዳን ጋር በነዳጅ ማስተላለፍ ሂደት ውስጥ የተፈጠረው አለመተማመን ሲሆን በተጨማሪም ነዳጁ ከሚመረትበት አንስቶ እስከ ጅቡቲ ወደብ ያለው እርቀት ከዚህ ቀደም ፓርት ሱዳን ካለበት አንፃር ሲታይ አጭር የመሆኑ ጉዳይ ነው፡፡
አዲሱ ፕሮጀክት ተግባራዊ ሲሆን ኢትዮጵያ ነዳጅን በሚመለከት ያላት ከፍተኛ ጥገኝነት ሰየተሻለ ጠቀሜታን እንድታገኝ መርዳቱ ሁለተኛው ምክንያት ነው፡፡ በነዳጅ ማስተላለፊያ ቱቦው አማካኝነት የኢትዮጵያ መንግስት ግዛቱን በመፍቀዱ የሚያገኘው የኪራይ ውል እንደተጠበቀ ሆኖ ፕሮጀክቱ በነዳጅ ላይ ያለንን መተማመኛ ከረጅም ዓመት እቅድ አኳያ አስተማማኝ ያደርግልናል፡፡ እነዚህን አካሄዶች በስርዓት መያዝ ከተቻለ የደቡብ ሱዳን ወደ ቀጠናው መቀላቀል እውነትም ለአገራችን በረከትን ይዞ ይመጣል ብለን ተስፋ እንድናደርግ ይረዳናል፡፡
ስጋቶች
ጋምቤላንና ደቡብ ሱዳንን በሚያዋስነው የድንበር አካባቢ ያለው ቀጠና ከረጅም ጊዜያት አንስቶ በተለያዩ ምክንያቶች ግጭትና ብጥብጥ ያልተለየው እንደነበረ የተለያዩ ፀሐፊያን ባሰፈሯቸው ድርሳናት ላይ ገልፀዋል፡፡ በእዚህ አካባቢ መነሻቸውን ላደረጉ ግጭቶች የተለያዩ ምክንያቶች ማቅረብ ቢቻልም በጥቅሉ መሰረታዊ ምክንያት የሚባሉትን አንዳንድ እውነታዎች በሦስት የተለያዩ ደረጃዎች ከፋፍለን ማስቀመጥ እንችላለን፡፡ ቀዳሚው ምክንያት በጋምቤላ ክልል ውስጥ የሚነሱ ግጭቶች እና አለመግባባቶች ብሎም የለየላቸው ጦርነቶች በክልሉ ውስጥ በሚገኙ ብሔሮች መካከል መነሻውን የሚያደርግ ሲሆን ሁለተኛው ምክንያት በክልሉ ውስጥ የሚገኙ አንዳንድ ብሔሮች ከማዕከላዊው የፌዴራል መንግሥት ጋር የሚፈጥሩትን አለመግባባት ተከትሎ የሚከሰተው ግጭት ነው፡፡ ሶስተኛው የግጭት ምክንያት ድንበር ተሻጋሪ ምንጭ ያለው ነው፡፡ ይኸውም የጋምቤላን ክልል ታኮ ባለው የደቡብ ሱዳን ድንበር አካባቢ የሚኖሩ የሌላኛዋ አገር ዜጎች የተፈጥሮ ሀብትን ከጋምቤላ ነዋሪዎች ጋር ለመጋራትና በሀገራቸው የሚቀሰቀሱ የተለያዩ ግጭቶችን በመሸሽ ድንበር አቋርጠው የሚገቡ ስደተኞች ከነዋሪዎቹ ጋር የሚፈጥሩት ግጭት ነው፡፡
ደረጄ ፈይሳ የተባሉ በጋምቤላ ክልል ዙሪያ ሰፊ ጥናትና ምርምር ያደረጉ ፀሐፊ ከላይ የጠቀስኳቸውን ተለዋዋጭ የግጭት ምክንያቶች ዘርዘር አድርገው ያስቀምጡታል፡፡ “A National perspective on the conflict in Gambella” በሚለው ጽሁፋቸው በተለያዩ ጊዜያት በጋምቤላ አካባቢና በደቡብ ሱዳን ድንበር አካባቢ የሚነሱ ግጭቶች አምስት መሰረታዊ መነሾ እንዳላቸው ያትታሉ፡፡
ቀዳሚው በጐሳዎች መካከል የሚነሳ የግጭት ነው፡፡ ይህ ትንተና በጋምቤላ ውስጥ በሚኖሩ የተለያዩ ብሔሮች መካከል የሚነሳውን ግጭት ይመለከታል፡፡ ለዚህ መሰሉ ግጭት ምክንያቶች የተለያዩ ቢሆኑም በተለይ የተፈጥሮ ሀብት ክፍፍል፣ አንዱ ብሔር ሌላኛው ብሔር በሚኖርበት አካባቢ የሚያደርገው ሰፈራ፣ በብሔሮች መካከል የሚከሰቱ የእርስ በርስ አለመግባባቶች በዋነኝነት ተጠቃሽ ምክንያቶች ናቸው፡፡ በክልሉ ከሚገኙት ብሔሮች መካከል ኑዌሮች እና አኙዋኮች በእንዲህ አይነት ግጭት በተደጋጋሚ ተጠቃሽ ናቸው፡፡
በጐሳ መካከል የሚነሳው ግጭት ሁለተኛው ምክንያት ነው፡፡ በክልሉ ውስጥ የሚገኙ ብሔሮች ከእርስ በርስ ግጭት አልፎ በውስጣቸው በያዟቸው ጐሳዎች መካከል የሚነሳው ግጭት ሌላኛው የቀውስ ምክንያት ነው፡፡ በጐሳ መካከል ለሚነሳው የእርስ በእርስ ግጭት በዋናነት ከሚቀመጡት ምክንያቶች መካከል የፖለቲካ ውክልና ለማግኘት የሚደረግ ፉክክር (በመጀንገር)፣ የተፈጥሮ ሀብትን በበላይነት ለመቆጣጠር ሲባል (በኑዌር)፣ ይጠቀሳሉ፡፡
ሌላኛው አገር በቀልና ህዳጣን በሚባሉት ዜጎች መካከል የሚነሳው ግጭት ሦስተኛው ነው፡፡ ጋምቤላ በማዕከላዊው መንግስት የግዛት ማስፋፋት ፖሊሲ ስር ከመጠቃለሏ በፊት በአካባቢው የነበሩ ብሔሮች በአንድ ወገን አገር በቀል (Natives) የሚባል ስያሜ ሲሰጣቸው፤ ግዛት ማስፋፋቱን ተከትሎ የሰፈሩና በንግድና በኋለኛው ዘመን በተካሄደዱ የሰፈራ ፕሮግራሞች አማካኝነት ወደ አካባቢው የመጡ ‹‹ሰፋሪዎች›› (Migrants) መካከል በቦታ ይዞታና የክልላዊ ማንነትን ጥያቄ መሰረት ያደረገው አለመግባባት ሌላው የግጭት መስመር ነው፡፡
ማዕከላዊ መንግስት በክልሉ ከሚገኙ ብሔሮች ጋር በሚፈጠረው አለመግባባት የሚከሰተው ግጭት አራተኛው ምክንያት ነው፡፡ ጋምቤላ ውስጥ ከሚገኙ ብሔሮች መካከል ማዕከላዊው መንግስት በተለይ በተደጋጋሚ የግጭት ሂደቶችን ያሳለፈው እና አሁንም እያሳለፈ ያለው ከአኙዋኮች ጋር ነው፡፡ የአኙዋኮች ጥያቄ ፖለቲካዊ ይዘት ያለው ቢሆንም በተደጋጋሚ ችግሩን ለመፍታት መንግስት የሄደበት መንገድ ለችግሩ ዘለቄታዊ መፍትሄ ከመስጠት ይልቅ ይበልጥ እያጋጋለው ለመምጣቱ አሁንም ግጭቱ ላለመብረዱ ምስክር ነው፡፡
የመጨረሻው ምክንያት ድንበር ተሻጋሪ ግጭት የሚለው ነው፡፡በጋምቤላ ውስጥ ከሚነሱ ግጭቶች መካከል ድንበር ተሻጋሪው ግጭት ለየት ያለ ባህሪ አለው፡፡ ለዚህም ሁለት ምክንያቶችን ማስቀመጥ ይቻላል፡፡ አንደኛው በግጭቱ ተሳታፊ የሚሆኑት ብሔሮች በሁለት የተለያየ ሉዓላዊ አገራት ውስጥ የሚገኙ የመሆናቸው ሁነት ሲሆን ከዚህ በተጨማሪም ለግጭቶቹ መፍትሄ ለመስጠት የሚወሰዱ እርምጃዎች ችግሩን በቀላሉ የሚፈቱ አለመሆናቸውን መጥቀስ እንችላለን፡፡
ከላይ የተጠቀሱት በጋምቤላ አካባቢ በምክንያትነት የሚቀርቡ የግጭት መስመሮች ከዚህ ቀደም ተለምዷዊ በሆኑ የግጭት አፈታት ስልቶች መፍትሄ ሲበጅላቸው ቆይቷል፡፡ የማዕከላዊውም ይሁን የክልሉ መንግስት በመሰረታዊ የክልሉ ህዝቦች ቅሬታ በሚያቀርቡበት ወቅት ምላሽ ተደርገው የተወሰዱት ባልተመጣጠኑ የግጭት አፈታት እርምጃዎች ምክንያት የተለያየ ወቀሳ የደረሰባቸው ቢሆንም ለጉዳዩ እየሰጡ ያሉት ትኩረት ግን አሁም ድርስ እዚህ ግባ የሚባልና መፍትሄውም ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እርምት መስጠት የሚችሉ አለመሆናቸው እስከዛሬም ድረስ እነዚህ ቀውሶች ተሸክመናቸው እንድንጓዝ ተገዳናል፡፡
ደቡብ ሱዳን ከግጭት ጀርባ
የደቡብ ሱዳን በምስራቅ አፍሪካ አካባቢ ተጨማሪ አገር ሆና ብቅ ካለች ገና ለጋ እድሜ ላይ ነች ቢባልም ለወደፊቱ ግን በተለይ ጋምቤላን ታከው ለሚነሱ ግጭቶች የደቡብ ሱዳን ሚና እንደ ከዚህ ቀደሙ ከኢትዮጵያ ያነስና በቸልታ የሚታይ ይሆናል የሚል እምነት የለኝም፡፡ የኢትዮጵያ መንግስትም የጋምቤላን የግጭት ምክንያቶች ተንተርሶ እርምት ለመውሰድ ብሎም ግጭቱን ለማስታረቅ በሚጠቀምበት መሰረታዊ አካሄድ ዙሪያ ዳግም የተሻለ እና ከዚህ ቀደም ከሚከተለው የተለየ አካሄድ ማየት እንደሚገባው አምናለሁ፡፡
በአካባቢው በሚነሱ ግጭቶች ዙሪያ ለወደፊቱ የደቡብ ሱዳን እየተጠናከረች መምጣት የተለየ ትርጓሜ እንደሚኖረው ከወዲሁ መገመት ከባድ አይሆንም፡፡ ወደፊትም ደቡብ ሱዳን በአካባቢው የሚኖራት አስተዋፅኦ አንዳድ መሰረታዊ ምክንያቶችን ይዞ የሚነሳ ይሆናል የሚል እምነት አለኝ፡፡
በሁለቱ አገራት (በኢትዮጵያ እና በደቡብ ሱዳን) ውስጥ የሚኖሩ የድንበር ተጋሪ ህዝቦች መካከል በተደጋጋሚ ለሚነሱ ግጭቶች መሰረታዊ ምክንያቶች ጠቅለል አድርገን ማስቀመጥ እንችላለን፡፡ በዚህ አካባቢ ያሉ ዜጐች ዋነኛ የኢኮኖሚ ገቢያቸው (መተዳደሪያቸው) በከብት ማርባት ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ እነዚህ ህዝቦች ለከብቶቻቸው የግጦሽ መሬት እና ውኃ ፍለጋ ሲሉ የአንዱን ድንበር አቋርጠው በማለፍ የተፈጥሮ ሀብትን ለመጋራት የሚያደርጉት ሙከራ የግጭቱ አንዱ ምክንያት ሲሆን፤ ሁለተኛው ምክንያት በተለይም ከዚህ ቀደም እንደታየው ጋምቤላ ውሰጥ ባሉት ኑዌርና በደቡብ ሱዳን በሚገኙት የሙርኔ ህዝቦች መካከል የሚፈጠሩ አለመግባባቶች የሚያስከትሏቸው የሰው ህይወት መጥፋት ለግጭቶች መባባስ ተጠቃሽ ምክንያቶች ናቸው፡፡
ደቡብ ሱዳን ከዚህ ቀደም ለእንደዚህ አይነት ድንበር ዘለል አለመግባባቶች ትሰጠው የነበረው ትኩረት አናሳ ከመሆኑም በተጨማሪ ራሳቸውን ከሰሜኑ የሱዳን ክፍል ለመገንጠል ያደረጉ የነበረው መራራ ትግል ደቡብ ሱዳንን በድንበር አካባቢ ለሚነሱ አለመግባባቶች ዋጋ እንዳትሰጥ አድርጓታል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ኢትዮጵያ በታሪክ ደቡብ ሱዳን ነፃ አገር እንድትሆን ያደረገችውን አስተዋፅኦ ከግምት ስናስገባ ለግጭቶቹ ትኩረት ሰጥቶ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ለመነታረክ የሚደረግ ማንኞቹም ሙከራዎች ከጥቅማቸው ይልቅ የሚያስከትሏቸው ኪሳራዎች መብዛታቸው ሌላኛው ለኢትዮጵያ የጠቀመ የማሰሪያ ፖለቲካ ካርድ ነበር፡፡
ጥያቄው ይሄ የፖለቲካ ካርታ እስከመቼ ያጫውታል? የሚለው ነው፡፡ ደቡብ ሱዳን ከዛሬ ነገ እየጠነከረች ስትመጣ ለዜጐቿ የምትሰጠውም ትኩረት የዛኑ ያህል እየጨመረ መምጣቱ አይቀርም፡፡ ‹‹በፖለቲካ ዘላቂ ወዳጅም ይሁን ዘላቂ ጠላት የለም›› የሚለው መርህ ተግባራዊ መሆን ሲጀመር፤ አልፎም ‹‹አገራት በአለም አቀፍ መድረክ በማንኛውም የሉዓላዊነት መስፈርት እኩል ናቸው›› የሚለው መርህ በተግባር ሲተረጎም ደቡብ ሱዳን ለዜጐቿ ጥበቃ እና ከለላ ለማድረግ በሚል ከአገራችን ጋር የተካረረ ግጭት ውስጥ ልትገባ የምትችልባቸው አጋጣሚዎች ይፈጠራሉ፡፡
በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን ድንበር በዘላቂነት ከተለያዩ ድንበር ዘለል አደጋዎች ለመጠበቅ ሊወሰዱ የሚገባቸው ቅድመ ጥንቃቄዎች መኖር እንደሚገባቸው ሊሰመርበት ይገባል፡፡ ለዚህም ቀላል እና አፋጣኝ ወቅታዊ እርምጃዎች ሊሰጥባቸው የሚገቡ የመፍትሄ አቅጣጫዎችን ማስቀመጥ ተገቢ ነው፡፡ የማዕከላዊውም ይሁን የክልሉ መንግስት አስቀድሞ በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን የድንበር ወሰን ጥርት ባለና ሁለቱንም ሊያግባባ በሚችል መልኩ ከደቡብ ሱዳን ጋር የመግባቢያ ሰነድ ተዘጋጅቶ ወደ ትግበራ መግባት ቀዳሚው ሲሆን (በሁለቱ አገራት መካከል ድንበርን በሚመለከት ያሉትን አንዳንድ መሠረታዊ ነጥቦች ለመረዳት ዶ/ር ወንደሰን ተሾመ የፃፉትን ‹‹colonial Boundaries of Africa the case of Ethiopia’s Boundry with suda›› የሚለው ፅሁፍ መመልከት በቂ ነው፡፡)፤ በሁለቱ አገራት አዋሳኝ ድንበር ላይ ባሉ ዜጐች መካከል የሚነሱትን አለመግባባቶች በባህላዊው የግጭት አፈታት መንገድ እልባት እንዲሰጣቸውና በቀጣይም ለግጭት የሚጋብዙ ምክንያቶችን ከምንጩ ለማድረቅ መስራት ይጋባል፡፡
በተጨማሪም በድንበሮች አካባቢ የሚኖሩ የሁለቱ አገራት ዜጎችን ኢኮኖሚ ከአርብቶ አደር ወደ ተረጋጋና የተሻለ ወደሚባለው የግብርና መር ኢኮኖሚ እንዲሻገሩ በማድረግ ግጦሽ መሬትን ፍለጋ በሚል ሰበብ ይከሰቱ የነበሩትን እንቅስቃሴዎች መግታት ከብዙ በጥቂቱ ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ መንግስትም እንደከዚህ ቀደሙ ሳይሆን የጋምቤላን ክልል በሚመለከት አዲስና የተለየ የፖሊሲ አቅጣጫ ትግበራ ማድረግ ይገባዋል፡፡ አለበለዚያ አዲሲቱ አገር ደቡብ ሱዳን ከበረከት ይልቅ ለቀንዱ አካባቢ ተጨማሪ መርገምት መሆኗ አይቀርም፡፡
“Irredentism”
ደቡብ ሱዳን በተጠናከረ መልኩ ወደ ቀጠናው እጇን እያሳረፈች ስትመጣ በቀጣይ ስጋት ልትሆን ትችላለች ብዬ ከማስብባቸው ምክንያቶች መካከል ከዚህ በፊት የገጠመን የሱማሌያ ተሞክሮ ሌላው ነው፡፡ ሱማሊያውያን ለረጅም አመታት በኢትዮጵያ ከተፈራረቁ ወሪዎች ጋር ደም አፋሳሽ ጦርነቶችን አድርገዋል፡፡ በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ከፍተኛ የታጠቀ ኃይል መኖሩ ዙሪያ ገባው አገራችን ክፍል ለተለያዩ ጥቃቶች እንድትጋለጥ አድርጓታል፡፡ በተለያዩ ጊዜያት በአገራችን ላይ ከሶማሊያ መንግስት የተቃጡብን ጦርነቶች ምክንያታቸው ተመሳሳይ ነው፡፡ በተደጋጋሚ ሶማሊያዊያኑ የግዛት ይገባኛል ጥያቄን በማንሳት በአገራችን ላይ ጦረነቶችን አውጀዋል፡፡ የግጭቶች መነሻ በኢትዮጵያ ስር ተጠልለው የሚገኙትን ሶማሌዎች የሚኖሩበትን አካባቢ (ኦጋዴን) በኢትዮጵያ መንግስት በጉልበት ተነጥቀናል የሚል ታሪካዊ ጥያቄን በማንሳት ነው፡፡ እነዚህ ኃይሎች ይህንን ጥያቄ መነሻ ምክንያት በማድረግ ‹‹ህዝባችን እና መሬታችንን እስካልተመለሰልን ድረስ ትግላችንን እንቀጥላለን›› የሚል ወጥ የሆነ አቋም ያራምዳሉ፡፡ ይህ ተደጋጋሚ ጥያቄ ለሶማሌያውያኑ የአንድ ወቅትና የአንድ ትውልድ ብቻም ሳይሆን የዘመናትም እስከመሆን ደርሷል፡፡ ይሄ በሶማሌያውያኑ የተሰነዘረው የመሬት ይገባኛል ጥያቄ (Irredentism) በቀጣይም ከደቡብ ሱዳን ሊቃጣ እንደሚችል መጠርጠር ተገቢ ነው፡፡ ይህንን ጥያቄ በደቡብ ሱዳንም ዘንድ ሊያስነሳ የሚችል ተመሳሳይ አይነት ተሞክሮ በጋምቤላና መኖሩን ማየት እንችላለን፡፡
አብዛኞቹ በጋምቤላ አካባቢ የሚኖሩ ብሔሮች በአንድም ይሁን በሌላ ከደቡብ ሱዳን ጋር የሚያመሳስሏቸው የተለያዩ ነገሮች አሉ፡፡ በተለይ በህዝብ ለህዝቡ ግንኙነት ዙሪያ ኑዌሮች እና አኙዋኮች ቤተሰቦቻቸውን ደቡብ ሱዳን አስቀምጠው የመጡ ናቸው፡፡ ረጅም አመት ያስቆጠረው የሱዳን እርስ በርስ ጦርነት ለብዙ የደቡብ ሱዳን ነዋሪዎች ከቀያቸው መፈናቀልና በጋምቤላ ቋሚ ኑሮ ለመጀመር አይነተኛ አስተዋፅኦ አበርክቷል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የደርግ መንግስት ለደቡብ ሱዳን ይሰጥ በነበረው ቀጥተኛ ወታደራዊ እርዳታ ምክንያት ከጋምቤላ ተቆርሶ በተሰጠው መሬት ላይ ደቡብ ሱዳናውያኑ ወታደራዊ ማዘዣ ጣቢያ ከፍተው ይጠቀሙ እንደነበር ይታወቃል፡፡
እነዚህ ምክንያች በቀጣይ ምን መዘዝ ይዘው ሊመጡ ይችላሉ? የሚለውን ማየት ተገቢ ነው፡፡የደቡብ ሱዳን መንግስት ይነስም ይብዛም ጋምቤላ ውስጥ ባሉ ብሔሮች መካከል ይፈጠሩ በነበሩ አለመግባባቶች እና ግጭቶች ውስጥ እጁ እንዳለበት የተለያዩ ፀሐፊያን ይስማማሉ፡፡ በተለይ በኑዌሮች እና አኙዋኮች መካከል ሲነሱ ከነበሩ ግጭቶች ጀርባ የደቡብ ሱዳን ጦር ኑዌሮችን በመርዳት ግጭቱን ያባብስ እንደነበር እነዚሁ ፀሐፊያን ያትታሉ፡፡ በቀጣይም የኢትዮጵያ መንግስት በአካባቢው ላይ በሚወስዳቸው ፖለቲካዊ እና ወታደራዊ እርምጃዎች ዙሪያ የደቡብ ሱዳን መንግሥት አንዳንድ አፀፋዊ እርምጃዎችን ሊወስድ ይችላል የሚል እምነት አለኝ፡፡
ጆን ያንግ “Armed groups along sudan’s Eastern frontiees: An over view and analysis” በሚለው ፅሁፋቸው ሁለቱን አገራት በሚያዋስነው ድንበር አካባቢ ለሚኖሩ ዜጐች አንዳንድ ማስተካከያዎች እስካልተደረጉ ድረስ ግጭቶቹ ተባብሰው ሊቀጥሉ እንደሚችሉ ያስረዳሉ፡፡ በተለይ በጋምቤላ አካባቢ ያሉ ዜጐች ወደ ድንበር የተጠጉ ከመሆናቸውም በተጨማሪ ከማዕከላዊ አስተዳደሩ እና ማህበረሰቡ ጋር ያላቸው ቁርኝት የላላ ነው፡፡ ከዚህ ውጭም በተለያዩ አጋጣሚዎች በክልሉ የተቀሰቀሱ ግጭቶችን ተከትሎ የተወሰዱባቸው እርምጃዎች ፊታቸውን ከማዕከላዊው አስተዳደር እንዲያርቁ አስገድዷቸዋል፡፡ ይህንና ሌሎች መሰል አጋጣሚዎች በጋምቤላ አካባቢ መከሰታቸው ደቡብ ሱዳን በቀጣይ በአገሪቷ ላይ ያላትን ተፅዕኖ ለማስፋት ልትጠቀምበት እንደምትችል መገመት ይቻላል፡፡ ከነዚህ ተጠባቂ ስጋቶች መካከል አንደኛው እንደ ሶማሊያ ሁሉ የግዛት ይገባኛል ጥያቄ የማንሳቷ ሁነት ነው፡፡ አብዛኛው የጋምቤላ ነዋሪ በደቡብ ሱዳን ውስጥ ከሚኖሩ ዜጎች ጋር ተመሳሳይ የሆነ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ያለው ከመሆኑ አንፃር የደቡብ ሱዳን መንግስት በቀጣይ የጋምቤላን መሬት ከራሳቸው ጋር ይቀላቀል ዘንድ ሴራ ሊሸርብ ይችላል፡፡ ለዚህም ሲል በክልሉ ውስጥ ከሚገኙ ህዝቦች መካከል ‹‹የተገፋው ማህበረሰብ›› በመንግስት ላይ እንዲያምፅ የማድረግ እንቅስቃሴ ውስጥ ሊገባ ይችላል የሚለው ቀዳሚው ሲሆን፤ ሌላኛው ስጋት የኢትዮጵያ መንግስት እንደከዚህ ቀደሙ በአኙዋኮች ላይ ወታደራዊ እርምጃ የሚወስድ ከሆነ ደቡብ ሱዳን በኢትዮጵያ ውስጥ በሚኖሩ ዜጐች ላይ የተቃጣውን ጥቃት ለመከላከል በሚል ድንበር ዘለል ድጋፍና ከለላ ልታደርግ ትችላለች የሚለው ስጋት ነው፡፡ይሄ ክስተትም ቀጣናውን ወዳልተፈለገ ብጥብጥ ይዞት ጭልጥ እንዲል ያደርገዋል፡፡
አዲሲቷን ደቡብ ሱዳን የምንመለከትበት የተለየ መነፅር ያስፈልገናል፡፡ ከመርገምቱ ይልቅ በረከቱን እንድንቋደስ የአገራችን መንግስት ብልጠት የተሞላበት ፖሊሲ ሊቀርፅ ይገባዋል፡፡

Filtered HTML

  • Web page addresses and e-mail addresses turn into links automatically.
  • Allowed HTML tags: <a> <em> <strong> <cite> <blockquote> <code> <ul> <ol> <li> <dl> <dt> <dd>
  • Lines and paragraphs break automatically.

Plain text

  • No HTML tags allowed.
  • Web page addresses and e-mail addresses turn into links automatically.
  • Lines and paragraphs break automatically.